የፈጠራው ባለቤት ግርማ ዘለቀ (ግርማ ስንዝሮ) ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

የፈጠራው ባለቤት ግርማ ዘለቀ (ግርማ ስንዝሮ) ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

e18ba8e18d88e18ca0e188abe18b8d e189a3e18888e189a4e189b5 e18c8de188ade1889b e18b98e18888e18980 e18c8de188ade1889b e188b5e18a95e18b9d የፈጠራው ባለቤት ግርማ ዘለቀ (ግርማ ስንዝሮ) ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩአቶ ግርማ ዘለቀ አላዩ ከአባታቸው ከአቶ ዘለቀ አላዩ ከእናታቸው ከወ/ሮ ዓለሚቱ ደጉ በባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ በደና ቀበሌ በ 1947 ዓ.ም. ተወለዱ ፡፡

እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ መጀመሪያ የቄስ ትምህርት ቤት ተከታትለው ወደ ዘመናዊ ትምህርት በዓጼ ሰርጸ ድንግል መላክ ሰገድ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከአንደኛ እስከ ስድሰተኛ ክፍል በመከታተል በመደበኛ ትምህርታቸው ውጤታማ ከሚባሉት ተማሪዎች ግንባር ቀደም የነበሩና ከልጅነታቸው ጀምሮ ልዩ ተሰጥኦ የነበራቸው በመሆኑ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን በትምህርት ቤት በማቅረብ መታዎቅ የጀመሩ ከልጅነት እድሜያቸው ጀምሮ ነበር፡፡

ከነዚህም ልዩ የፈጠራ ስራዎቹ መካከል በባህር ዳር ከተማ የሲኒማ ቤት ከመከፈቱ በፊት በወቅቱ ወወክማ ተብሎ ይጠራ በነበረው የወጣት ወንዶች ክርስቲያን ማህበር ቅጥር ግቢ ይታይ የነበረውን የሲኒማ ማሳያ መሳሪያ በመመልከት በራሳቸው ፈጠራ በካርቶንና በፕላስቲክ ማቴርያሎች ላይ ስእል በመሳል ለወጣቶች ፊልሞችን ያሳዩ ነበረ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የመካከለኛ ሞገድ ሬድዮ በመስራት ለመምህራኖቹና ለት/ቤት ጓደኞቻቸው በማሰማት ይታወቁ ነበር፡፡

በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቆይታቸው በወቅቱ ኤክስከርሽን በመባል ይታዎቅ የነበረውን ዓመታዊ የፈጠራ ስራ ውድድር ሁልጊዜ አዳዲስ ስራዎችን በመፍጠር ከራሳቸው ስራ ባሻገር እርሳቸው ያሉበትን ቡድን አሸናፊ በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደነበራቸውው ታሪክ ያስረዳል፡፡

ግርማ በ 1963 ዓ.ም. ከአስመራ ተግባረዕድ ኮሌጅ በኤሌክትሮኒክስ ሙያ ከተመረቁ በኋላ በ1964 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ቴሌቪዢን ከተቋቋመ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በፊልም ቴክኒሻንነት በቋሚነት ለመጀመሪያ ጊዜ ተቀጥረው ማገልገል ጀመሩ፡፡

በወቅቱ ባለ ቀለም ፊልም የመቅረጽ ተግባርን የሚያከናውን መሳሪያ ባለመኖሩ በጥቂት ጊዚያት ባካሄዱት ጥናት በራሳቸው የፈጠራ ስራ ይህንን ተግባር የሚያከናውን መሳሪያ በመፈብረክ ለቴሌቪዢን ጣቢያው በማቅረብ አድናቆትን ሲጠብቁ ያገኙት ምላሽ ከሚጠብቁት በታች ስለነበርና የሚረዳቸው ባለሙያና የስራ ሃላፊ በማጣታቸው እቃውን በመስኮት ወርውረው በመስበር ቅጥሩንም አቋርጠው ወጥተዋል፡፡

የንጉሱን አገዛዝ ስርአት በመገርሰስ የደርግ መንግስት ወደ ስልጣን ሲመጣ ከደርግ መንግስት ጋር መስማማት ስላልቻሉ ወደ ሳኡዲ አረቢያ በስደት በመሄድ ህይዎታቸውን ለመምራት ተገደዱ፡፡
በሳኡዲ አረብያ በነበራቸው ቆይታም ለአስር አመታት በሰለጠኑበት የኤሌክትሮኒክስ ሙያ ዘርፍ በታላላቅ ፋብሪካዎች ተቀጥረው በተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን በቆይታቸውም ሙያውን በዘመናዊ መንገድና በዓለም አቀፍ ደረጃ በታወቁ የቴክኖሎጂ ውጤት ማሽኖች እየታገዙ በበለጠ ማሳደግ ችለዋል፡፡
በወቅቱ በጀዳ ሃገር በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ቁጥር በመመልከት ለኢትዮጵያውያን ዋና ችግር የሆነውን የጤፍ እንጀራ መጋገሪያ ምጣድ ችግር የሚፈታ የፈጠራ ስራ አከናውነዋል፡፡

READ ALSO:   Census: A quarter of Japanese men unmarried at the age of 50

ለዚህም ለመጀመሪ ጊዜ አውቶማቲክ የእንጀራ መጋገሪ ማሽን ዲዛይን በማድረግና በመፈብረክ ለስራ አብቅተዋል፡፡
አቶ ግርማ ከደርግ መንግስት መውደቅ በኋላ የስደት ኑሮ በቃኝ በማለት ወደ ሃገራቸው በ1984 በመመለስ በተለያዩ የንግድና ኢንቬስትመንት ስራዎች ላይ ተሰማሩ፡፡ በዚያኑ ዓመትም ከወ/ሮ ማርታ ካሳ ጋር ትዳር በመመስረት ኑሯቸውን የተሳካ እንዲሆንና ባምሳያቸው በሙያ የተካኑ ተኪዎቻቸውን ለመፍጠር የሚያስችላቸውን መንገድ መከተል ጀመሩ፡፡

ከስደት መልስ በሃገራቸው ታዋቂ የሆኑ የፈጠራ ስራዎቻቸውን ማከናዎን ከጀመሩበት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መላው ኢትዮጵያዊ በስራቸው ያወድሳቸው ዘንድ ካበቋቸው የስራ ውጤቶች መካከልም በኢትዮጵያ በዓይነቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በመንገድ ላይ በቢልቦርድ የተለያዩ መልእክቶችን በጽሁፍና በምስል እየተሸከረከረ የሚያሳይ ፕሪዝማ ቪዢን የተባለ የፈጠራ ስራቸውን በ1986 ዓ.ም. በማከናዎን ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች ላይ በመትከል ችሎታቸውን ማሳየት የጀመሩ ሲሆን፤ በመቀጠልም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በቴሌቪዢን የሚያውቅና በሁላችንም አዕምሮ ተቀርጾ ያለውን በቀደምት ጊዜያቶች የልጅነት መማሪያ መጽሃፎቻችን ላይ የምናስታውሰውን ስንዝሮን በ1988 ዓ.ም. በአኒሜሽን በመስራት በቴሌቪዢን ማሳየት ቻሉ፡፡

የስንዝሮ አኒሜሽን ስራ ዋና ዓላማም በሃገር ውስጥ ላሉ ህጻናት የእንግሊዘኛ ቋንቋቸውን እንዲያሻሽሉ በውጭ ሃገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ህጻናት ደግሞ አማርኛ ቋንቋ እንዲማሩ በማዝናናት እንዲገለግል ነበር፡፡
በዚህ ስራቸው በየሃገሩ ላሉ ኢትዮጵያውያን የሰጧቸውን አድናቆት በመመልከት ስንዝሮን በአሻንጉሊት በፋብሪካ ተመርቶ ለህጻናት መጫዎቻ እንዲውልና በመላው ዓለም ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ያገኙት ዘንድ ይህንን ምርት የሚያመርት ፋብሪካ በአዲስ አበባ በ1990 ዓ.ም. ከፈቱ፡፡
ለረዢም ዓመታት በልብስ መደብሮችና ሱቆች እናያቸው የነበሩ የልብስና የአለባበስ ማስታዎቂያ ነጭ አሻንጉሊቶች በጥቁርና አፍሪካዊ መልክ ባላቸው አሻንጉሊቶች እንዲተኩና ሃበሾችና አፍሪካውያን በራሳቸው መልክ እንዲኮሩ አስቻሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ግርማ ዘለቀ የሚለው ስም በግርማ ስንዝሮ ተተካ፡፡

በዚያን ወቅት ስንዝሮን ወደ ውጭ ገበያ የመላክ ጥረትን በሙከራ ደረጃ ወደ አሜሪካና የተለያዩ የአውሮፓ ሃገሮች በመላክ አበረታች ውጤት መመልከት ቻሉ፡፡ ከዚህም በመነሳት ግርማ ስንዝሮ ያሻንጉሊት ፋብሪካው ኢንቬስትመንት ስራ የማምረት አቅሙ እንዲያድግ፤ ተጨማሪ ሌሎች ስራዎችን ለማከናዎን ብሎም የአሻንጉሊት ምርቱን ወደ ውጭ ገበያ ለማቅረብ አቅደው ሲንቀሳቀሱ ባጋጠማቸው የቢሮክራሲ ችግር ምክንያት ፋብሪካውን ጥለው ለሁለተኛ ጊዜ የስደት ህይዎትን ለመሞከር እንደገና ወደ አሜሪካን ሃገር በስደት ሄዱ፡፡
አሜሪካን ሃገር ከገቡ በኋላ በሜሪላንድ ግዛት ሲልቨር ስፕሪንግ ካውንቲ ኑሯቸውን በመከተም ለበርካታ የኢትዮጵያውን ስደተኞች ዋነኛ ችግር የሆነውን የጤፍ እንጀራ መጋገሪያ አውቶማቲክ ማሽን በአሜሪካን ሃገር ስታንዳርድ ደረጃ ዲዛይን አዘጋጅተው በማቅረብና በማስፈቀድ ብሎም መሳሪያውንም በመፈብረክ ለኢትዮጵያውያን አቅርበዋል፡፡

READ ALSO:   3 Firms Competing for IFRS Contract with Insurers Association

በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግስት በውጭ ለሚኖሩ ዲያስፖራ ዓባላት ባቀረበው የኢንቬስትመንትና ልማት ጥሪ መሰረት ግርማ ከአሜሪካን የስደት ህይዎታቸው በኋላ ቀሪውን እድሜያቸውን የሃገራቸውን ልጆች ተመልሰው በመምጣትና ሃገራቸው ላይ አብረዋቸው እየኖሩ ለማገልገልና በፈጠራ ስራዎቻቸውም የበለጠ በቅርብ ለማገዝ በትውልድ ከተማቸው በሆነችው ባህር ዳር በመምጣት በኢንቬስትመንት ተግባር ላይ ለመሰማራት በ2007 ዓ.ም. ወሰኑ፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ በኢንዱስትሪ ኢንቬስትመንት ተግባር ለመሰማራት የምስማርና የተለያዩ ከሽቦ የሚፈበረኩ የኮንስትራክሽንና የቢሮ እቃዎች ማምረቻ በእንግሊዘኛው አጠራር ዋየር ድሮዊንግ ፋብሪካ ለመገንባት በመወሰን ፕሮጀክት አቅርበው ቦታ ተሰጥቷቸው ፋብሪካውን በአጭር ጊዜ መገንባት የቻሉ ሲሆን ይህም ተግባራች በዛሬዋ ዕለት የህንጻ ግንባታው ተጠናቆ የማሽነሪ ግዢ ላይ ይገኛል፡፡
ይህ በእንዲህ እያለ ይህንን ፋብሪካ እየገነቡ ባሉበት ባለፉት 2 ዓመታት ቆይታቸው ግርማ ስንዝሮ ተወልደው ባደጉባት የባህር ዳር ከተማ ለአካባቢው ፈርጥ የሆነው የጣና ሃይቅ ሃብት በእንቦጭ አረም መወረሩንና መንግስትና ህብረተሰቡ ይህንን አረም ለማስዎገድ የሚያደርገውን ጥረት መመልከት በመቻላቸው የውሃ ላይ አረም አስዎጋጂ ድርጅትን ማቋቋም ቻሉ፡፡

ግርማ ስንዝሮ በባህር ዳር ቆይታቸው ወቅት ያላቸውን ልዩ የፈጠራ ችሎታ በመጠቀም በውጭ ዓለም ያዩትን የሃይቅ ላይ መዝናኛ ጀልባ ቴክኖሎጂ ለመስራት አቅደው 8 ሰው የሚይዝ በዓይነቱ ልዩ የሆነ በጣናና በሌሎች የሃገሪቱ ሃይቆች ላይ የሚንሳፈፉ የመዝናኛ ጀልባ ለማምረት የዲዛይን ስራ አጠናቀው አንድ ጀልባ ለሙከራ ምርት አከናውነው ሃይቅ ላይ ለመሞከር በዝግጅት ላይ ነበሩ፡፡
ግርማ ከነዚህ በተጨማሪ በባህር ዳር ቆይታቸው የፈጠራ ስራ ውጤቶቻቸውን በማምጣት ለከተማዋ ይሆን ዘንድ ያቀዷቸው አያሌ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች ነበሯቸው፡፡
ግርማ ስንዝሮ እየገነቡት ያለውን ፋብሪካ አጠናቀው ባለቤታቸውንና ልጆቻቸውን ለምረቃ በድንገት ጠርተው ሊያስገርሟቸው እንዳቀዱ ባልታሰበና በድንገተኛ አደጋ ህክምና ላይ በፈለገ ህይዎት ሆስፒታል ለአምስት ቀናት ሰነበቱ፡፡ ጓደኞቻችና ወዳጆቻቸውም ስንዝሮን ሲያስታምሙ ከቆዩ በኋላ ህክምናቸው ለውጥ አለማምጣቱን ሲያዩ ለ ባለቤታቸው ለወ/ሮ ማርታ ካሳ እንዲነገራቸውና ከአሜሪካን ሃገር እንዲመጡ መልክት ለመላክ ከሁለት ቀን በፊት ተገደዱ፡፡
ባለቤታቸው ወ/ሮ ማርታ ካሳ መልክቱ እንደደረሳቸው ባህር አቋርጠው ከአሜሪካን ሃገር በመምጣት ባለቤታቸው በሆስፒታል በህክምና እየተረዱ ለአይነ ስጋ በቅተው ለተሸለ ህክምና ያበቋቸው ዘንድ ትናንትና እኩለ ቀን ባህር ዳር አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ግርማ ግን እልፈተ ህዎታቸው ተሰምቷል፡፡

READ ALSO:   US Condemns Deadly Ethiopia Clashes

ሟቹ የፈጠራ ሰው ግርማ ስንሮም ባጋጠማቸው ድንገተኛ አደጋ ምክንያት በፈለገ ህይዎት ሆስፒታል በህክምና ሲረዱ ቆይተው ህመመቸው ሊሻላቸው ባለመቻሉ በተወለዱ በ63 አመታቸው መጋቢት 10 ቀን 2010 ዓ.ም. እኩለ ቀን ላይ ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ግርማ ስንዝሮ ባለትዳርና የአንድ ወንድና የሶስት ሴት ልጆች በድምሩ የአራት ልጆች ዓባት ነበሩ፡፡

ምንጭ: አማራ ብዙሀን መገናኛ ኤጀንሲ (አብመድ)

Categories: News
Tags: News

About Author

Write a Comment

Your e-mail address will not be published.
Required fields are marked*